This is an article from a Toronto resident , Mr. Alemayehu Asfaw. He urges the Ethiopian community in Toronto to work together to create a stronger community with a better future .
“ከአድማስ ባሻገር”
ለኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ማሳሰቢያ በቶሮንቶና አካባቢው
ክቡራትና ክቡራን በምንኖርበት አገር ካናዳ ከሞላ ጎደል ነፃነታችን በሚገባ ተከብሮ መብታችን ተጠብቆ ዲሞክራሲና የሰው የመኖር ህልውና የሚከበርበትና የህግ የበላይነት የሚንጸባረቅበት በመሆኑ ደስታ ሊሰማን ይችላል። ከዚያም በላይ እያንዳንዳችን በግላችን ለደረስንበት የትምህርት ደረጃም ሆነ የሥራ ብቃት ብዙዎቻችን እርካታ ሊሰማን ይችል ይሆናል።
በበኩሌ ግን የተዘነጋና ችላ የተባለ አንድ ጉዳይ ያለ ይመስለኛል። ይኽውም በጋራ ሆነን በሕብረት ልናደርጋቸውና ልንንከባከባቸው የሚገቡን ነገሮች ላይ ምንም ዓይነት ተሳትፎና መውሰድ የሚገባንን ሃላፊነትና እርምጃዎች ሁሉ ወደኋላችን በመተው ጉዞ እያደረግን ይመስለኛል። ለዚህ ጉዳይ ሁላችንም፥ በሥራ በሕክምና በንግድ በትራንስፖት በትምህርትና በሌላ ማንኛውም መስክ የተሰለፍን የኢትዮጵያውያን ወገኖች የሚጠበቅብን ከፍተኛ ሃላፊነት ያለው ጉዳይ መኖሩ የማይካድ ነው። በዚህም ያለንበት አገር ሕብረተሰብ ልናበረክት የሚገባንን አስተዋጽዖ በትኩረት የሚጠብቅብን መሆኑን መገንዘብ ይገባል።
እዚህ ላይ ያለፈ ታሪካችንን ማስታወስ ጠቃሚ ሳይሆን አይቀርም። ያለፈ ታሪኩን የማያስታውስ ወይም የዘነጋ ሕዝብ እድገት አያመጣም። የጥንት አባቶቻችን (አባቶቻችን ስል እናቶቻችንንም ይጨምራል) የራሳቸው ሥልጣኔ የራሳቸው ባህል የራሳቸው ሃይማኖት ቋንቋ ጽሑፍ አለባበስ አበላል አጠጣጥና ሥነሥርዓት የነበራቸው እንደነበሩ የታወቀ ነው። በዚሁም የኢትዮጵያ የጥንት ቅርስ የሆኑ ሃውልቶችና መዛግብት በዓለም ደረጃ ከመታወቃቸውም በላይ የዓለም ቅርሳት ሆነው እንዲጠበቁ ሆነዋል።
አባቶቻችን በፍጹም ጥቃት አይወዱም። በዚህም ምክንያት ነው አገራቸውን በተደጋጋሚ ከሚመጣ ጠላትና ወራሪ ጋር እየተዋጉና እራሳቸውን እየሰዉ ለምዕተ ዓመታት እየተዋጉ አገራቸውን ሳያስነጥቁ ኖረዋል። ይህ ዓይነቱ ታሪክ በፍጹም በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ያልታየ ነው። አባቶቻችን አገራቸውን ከቅኝ ተገዢነት ነፃ አድርገው ከትውልድ ወደ ትውልድ አስተላልፈው ለእኛ አቆይተውልናል።
ከዚህም በላይ አባቶቻችን ለቤተሰባቸውና ልጆቻቸው በጣም ክብር ስለነበራቸው ነበር ከራሳቸው ይልቅ ለልጆቻቸው በማሰብ አገሩም መሬቱም ለባእድ እንዳይሄድ ጥቃትን ሲከላከሉ የቆዩት። ዓፄ ቴዎድሮስ ጄኔራል ናፒየር በጦርነት ቢያሸንፋቸውም እጅህን ስጥ ሲሏቸው፣ “እጅህን ስጥ ይለኛል እጄ እሳት መሆኑን አላወቀም” ብለው ራሳቸው ሽጉጣቸውን ጠጥተው ሞቱ። ምናልባት ዓፄ ቴዎድሮስ ይህን ታላቅ መስዋእትነት ባይከፍሉ ኖሮ ኢትዮጵያም እንደሌሎቹ አፍሪካ አገሮች ሁሉ ለብዙ ዓመታት በቅኝ ተገዢነት ምናልባት ሳትማቅቅ አትቀርም ነበር ማለት ይቻላል።
እዚህ ላይ እንግዲህ አባቶቻችን እኛን አስተምረው ከእነሱ እጅግ በተሻለ ሁኔታ እንድንኖር ካደረጉ እኛስ ምን ማድረግ ይገባናል ብለን እያንዳንዳችን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። እኛም ልክ አባቶቻችን እንዳደረጉት በሕብረት አንድ ሆነን እየተረዳዳን ተከባብረን የወደፊቱን በማሰብ ለልጆቻችን ባሉበት አገር ጥቃት ሳይደርስባቸው በሕብረታቸው ጠንካራ አንድነት ኖሯቸው መኖር እንዲችሉ ማመቻቸት ኃላፊነት መውሰድ ግዴታ ይሏል።
በምንኖርበት አገር ሌሎች ማኅበራት የተሻለ ሥራ እየሠሩ እየዳበሩና እየተሻሻሉ ተደማጭነታቸውን በልቀት እየጨመሩ ሲሄዱ አይናችንን ከፍተን ማየት አስፈላጊ ይመስለኛል። እዚሁ እምንኖርበት ከተማ ውስጥ ስንት ጊዜ ነው “አንድ ኢትዮጵያዊ ባቡር ሥር ወድቆ ራሱን አጠፋ” እየተባለ እንደወሬ የምንሰማው? ስንት ወጣቶች ይሳካልናል ብለው ስንት አገር ዞረው እዚህ ከደረሱ በኋላ አልሳካ ብሏቸው የአእምሮ በሽተኛ የሚሆኑት? ስንት አዛውንት ናቸው እርዳታ የሚፈልጉ? ከዚህም በላይ ቁጥራቸው ከመጠን ያለፈ ኢትዮጵያውያን በየአገሩ፥ ጣሊያን እስራአኤል ግብጽ ሳውዲ ሊቢያ ሱዳን ኬንያ ዩጋንዳ ደቡብ አፍሪካ ሌሎችም አገሮች በሬፉጂ ካምፕ በችግር ለዓመታት የሚሰቃዩ እንዳሉ ሁላችንም እናውቃለን። ምናልባት በዚህ ችግር ውስጥ ዛሬ እዚህ ያለን ሰዎች ብዙዎቻችን ሳናልፍ አልቀረንም። ለእነዚህ ሰዎች የማናስብ ከሆነ ወይም ችላ ብለን ችገሩን እንደሌለ የምንቆጥር ከግሆነና በሕብረት ሆነን በተግባር የሚጠበቅብንን የማንፈጽም ከሆነ እያንዳንዳችን ከግል ጥቅማችን ውጭ መጠየቅ የማንፈልግ መሆኑን እሚያረጋግጥ ስለሚሆን ሌላው ቢቀር የምንኖርበት አገር ሕብረተሰብ ይታዘበን ይሆናል። ያም ብቻም አይደለም ለወደፊቱ ደግሞ ለራሳችንም ሆነ ለልጆቻችን ተደማጭነታችን እንዲኮስስ መንገዱ የምንጠርግ እንዳይሆን ያሰጋል። ተደማጭነቱ አነስተኛ የሆነ ሕብረተሰብ እምብዛም ክብሩ ላይጥበቅ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ተሰልፈን ከተማ ወጥተን ወያኔን ስናወግዝ ይታያል። ወያኔን መቃወሙ ትክክል አይደለም ማለት ሳይሆን አጠገባችን ላሉ ችግሮች መፍትሔ ማድረጉ ሳያቅተን ልንተባበር ፈቃደኞች ባለመሆናችን ብቻ ችላ ብለን ስናየው የሌላው ኮሚዩኒቲ ሰዎች ይገረሙብን ይሆናል።
በበኩሌ የማሳስበው በጣም ቀላል ይመስለኛል፥
1. እዚህ አገር የሚኖር ማንኛውም የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆነ ግለሰብ ሁሉ ከወገኖቹ ጋር ሕብረት እንዲያስብና እንዲፈጥር። በማንኛውም ረገድ ሁላችንም የተለያየ አስተሳሰብና እምነት ሊኖር ይችላል። የጋራ ጥቅማችንንና ተደማጭነታችንን ለማስከበር በአንድነት መቆም ተገቢ ይመስለኛል።
2. የዛሬውን የግል ኑሯችንን ብቻ ከማሰብ ይልቅ ከዚያም ባሻገር በየትም ቦታ ቢሆን ለልጆቻችንና ለዎገኖቻችን ምንም ጊዜ ሳንቆጠብ በተጨማሪ ማሰብ ይገባናል፣ ኃላፊነትም አለብን።
3. አንዳንድ ሰዎች ለሕብረተሰባችን ሲያገለግሉ ስናይ ሥራቸውን ከማቃለልና ስማቸውን ከማጥፋት ይልቅ እነሱን ማበረታትና ከነሱ ጋር ለመተባበር መሞከር ተገቢ ጉዳይ ነው።
4. ይህን መመሪያችን አድርገን ጠንካራ ሕብረተሰብ ከፈጠርን በማንኛውም ቦታ ራሳችንን ማስከበር እንችላለን፤ ለልጆቻችን የተመቻቸ የኑሮ ሁኔታ እናመቻቻለን፤ በአገርቤትም ሳንነጣጠል እርዳታ ማድረግ አያቅተንም።
እግዜር ይስጥልኝ፤ አመሰግናለሁ።
ከዓለማየሁ አስፋው/ ቶሮንቶ
Photos by Yohannes Ayalew
The viwes expressed in this article are that of the writer and do not necessarily reflect the views of ethiofidel.com.