ኢትዮጲያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ ካናዳ በይፋ ተከፈተ
ቅዳሜ ፌብሯሪ 16፣ 2019 በከተማችን በቶሮንቶ በ958 ብሮድ ቪው አቨኑ በተካሄደ ይፋዊ ቻፕተሩን የመመስረቻና የትረስት ፈንዱን አላማ የማስተዋወቂያ ዝግጅት በአይነቱ የመጀመሪያው በተሳካና በተዋጣለት መልኩ መከናወኑ ተዘግቧል። በእለቱ ከዋናው የትረስት ፈንድ ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ከአሜሪካ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገ/ማሪያም፣ አቶ ሄኖክ ተስፋዬ፣ አቶ ብስራት አክሊሉ፣ ሉሊት እጅጉ፣ የተገኙ ሲሆን ከተሳታፊዎች ለቀረቡ የተለያዩ የተለያዩ ጥያቄዎች ሰፋ ያለ ምላሽና መብራሪያ በመስጠት በህዝቡ ዘንድ የሚመላለሱ ስጋቶችንና ጥርጣሬዎችን ለመቅረፍ መድረኩ እድል ፈጥሯል ተብሏል።
የትረስት ፈንዱ ዋና አስተባባሪ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገ/ማሪያም ካናዳ በቻፕተር ደረጃ በአይነቱ የመጀመሪያው መሆኑንና ከጠበቁት በላይ መሆኑን የገለፁ ሲሆን የልኡኩ አባላትም እጅግ መደሰታቸውን ገልፀው እስካሁን ባለው ገንዘብ የመሰባሰብ ሂደትም ካናዳ ከአሜሪካ ቀጥሎ ብዙ ገንዘብ በመለገስ ተጠቃሽ መሆኗን አብስረዋል። ነገር ግን አሁን ካለው አቅምና ከሚጠበቀው አንፃር እጅግ አነስተኛ መሆኑን በመግለፅ ልገሳው ተጠናቅሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል። የካናዳ በተለይ የቶሮንቶና አካባባቢዋ ነዋሪም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብቷል።
ቻፕተሩም ዝግጅቱ እጅግ የተሳካ መሆኑን በመግለፅ በካናዳ በአጠቃላይ ያሉ እንቅስቃሴዎችን በማስተባበር በተለያዩ አካባቢዎች ሰፊ ስራ ወደ ፊት እንደሚሰራ አስታውቋል። ቻፕተሩን በማስተባበር የሚመሩት አቶ ዩሱፍ ኡመር፣ ወ/ሮ እስከዳር እምሻው፣ ሊቀ ካህናት ምሳሌ፣ፍሰሃ ያእቆብ፣ አቶ ኢብራሂም፣ ዘሪሁን አዲሱ፣ አቶ ሄኖክ አበበ ናቸው። በእለቱ በካናዳ የኢትዮጲያ ኤምባሲ ከኦቶዋ ኃላፊዎችና ተወካዮችና የልዩ ልዩ የህብረተሰብ ወኪሎችና የሀይማኖት አባቶች በእንግድነት ተገኝተዋል። በዝግጅቱ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ እገዛና ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና ና እውቅና ተሰጥቷል።
ምንጭ ህዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ፣ ዘሪሁን አዲሱ