New Ethiopic Alphabets Book from Saba Alemayehu

Here is my interview with Saba Alemayehu who published a book for kids to learn Ethiopian Alphabet . Saba reflected about her book with ethiofidel.

ሳባ ኣለማየሁ ትባላለች የ ቶሮንቶ ካናዳ ነዋሪ ናት ። ለ በርካታ ኣመታት የ ኣገራችንን ባህል እና ጭፈራ ኣስተዋውቃለች ።

ኑቬል ኤክስፖዜ የተሰኘ የውዝዋዜ ቡድን በመምራት በ በርካታ ካናዳ ኣቀፍ መድረኮች ላይ ዝግጅቷን ኣቅርባለች። ኣሁን ደግሞ ሳባ የ ግራፊክስ ዲዛይን ሙያዋን ተጠቅማ ልጆች የግእዝ ፥ኣማርኛ እና ትግርኛ ፊደላትን በቀላል ስእላዊ መግለጫ የሚማሩበት መጽሃፍ ኣዘጋጅታ ለገበያ ኣብቅታለች ። ሳባን ስለመጽሃፏ ለ ኢትዮፊደል ሚዲያ ኣነጋግሪያታለሁ እንድታነቡት እጋብዛለሁ

ስለ አዲሱ መጽሐፍሽ ንገሪን፣ መጽሐፍሽን ልዩ የሚያደርገው ነገር ምንድነው?

                      
ጆኒ በቅድሚያ ለኢትዮፊደል ተከታታዮችህ ስለ አዲሱ መጽሐፌ “Ethiopic Alphabets : የኢትዮጵያ ሆሄያት (ፊደላት)”. እንዳስተዋውቅ ጊዜና ቦታ ስለሰጠኸኝ በጣም አመሰግናለሁ፡፡

በእርግጥ ፊደላቱ የኔ አይደሉም ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት የነበረ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ማለትም የግዕዝ፣ የአማርኛ እና የትግርኛ ጽሑፎች ቅርሶች ወይንም ውርሶች ናቸው። እኔ ሆሄያቱን ወይንም ፊደላቱን ለማስታወስ፣ ለማንበብና ለመጻፍ እንዲቀል መንገድ ነው የፈጠርኩት ።ይህ በደንብ በግልጽ እና በተደራጀ መልኩ የቀረበው ሥራ ፊደላቱን በቀላል ለማስታወስና ለመለየት የሚያስችል ከመሆኑም በላይ በቀለምና በንድፍ ማስታወስ እንዲቻል አድርጌአለሁ

በተጨማሪም የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የተለየ ለሆኑት ይረዳ ዘንድ  የላቲን የድምጽ አወጣጥ አለውና ፊደሎቹን በቀላሉ ለመጥራት ይረዳል። በተለይ ልጆች እየተጫወቱ እና እየተዝናኑ ሊማሩበት ይችላሉ።


መጽሐፉን ለማዘጋጀት ሃሳቡ እንዴት መጣልሽ?

ልጄ መናገር የጀመረችው ዘግይታ በመሆኑ እንግሊዝኛ  ከአማርኛጋ በአንድ ላይ ለማስተማር በካናዳ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ ነው። ልጄ በምስል በቀላሉ እንደምትረዳ ቀደም ብለን ስላስተዋልን በዚህ መንገድ ማስተማሩን ቀላል መንገድ ሆኖ አገኘነው። ስለዚህ ልጄ ተጨማሪ የመግባቢያና የመማሪያ መንገድ እንዲኖራት የኢትዮጵያን ሆሄያት ብታውቅና ብታነብ ይረዳታል ብዬ አሰብኩ።    .

ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ በእንግሊዝኛ የተዘጋጁ ብዙ መፅሐፍት፣ መጫዎቻዎች፣ ትዕይንቶች፣ ወዘተ አሉ።በአንፃሩ ግን በአማርኛ ነጭ የፊደል ሰሌዳ ላይ መጻፍና ደጋግሞ ማዜም ረዥምና አሰልቺ ነው። ልጅ ሳለሁ እኔ በዚህ  መንገድ ነው የተማርኩትና መቼ አልቆ በወጣሁ እያልኩ ነበር የማስበው

ስለዚህም ልጄ የምትወዳቸውን ቀለማትና ንድፍ መሞከር የተሻለ ነው በሚል ኃሳብ ተጀመረ።


መጽሐፉን ስታዘጋጂ ማንን እያሰብሽ ነበር? መፅሐፉ የተዘጋጀው ለማነው?
በመሠረቱ መፅሐፉ አማርኛ፣ ትግርኛና ግዕዝ ለመማር ለሚጀምር ሁሉ እንዲሆን የተዘጋጀ ነው። በተለይ ደግሞ በውጭ የተወለዱ የተለመደው የፊደል ገበታን ለመማር አስቸጋሪ ለሆነባቸው ኢትዮጵያዊ ሕፃናት የበለጠ ጠቃሚ የሆነ ነው። ይህ የመማሪያ መፅሐፍ ተነባቢና በቀላሉ ሊዋሐዱ በሚችሉ ቀለማትና ንድፍ የተሠራ ነው። የላቲን ድምጽ አወጣጦቹም በውጭ ለሚኖሩት ለእንግሊዝኛ ተናጋሪ የኢትዮጵያውያን ልጆች ለማንበብ እንዲቀላቸው ያደርጋል

እስካሁን ድረስ ኣንባቢዎች ምላሽ እንዴት ነው?

ቀደም ብዬ ቤት ውስጥ ስጠቀምበት የቆየሁ ስለሆነ ከልጆቼ በጣም ጥሩ ምላሽ ነው ያገኘሁት። ከልማዳዊው መማሪያ ይልቅ ይኼኛው መማርን አስደሳች አድርጎላቸዋል። ትልቋ ልጄ ከኔ ሁሉ በተሻለ በቃሏ ኣጥንታዋለች ።ለማንበብና ለመጻፍም ጥሩ ማገናዘቢያ ሆኗቸዋል

መማሪያው አዲስ እንደመሆኑና ማስተዋወቅም ባለመጀመሬ ሌሎች የሚሰጡትን አስተያየት አላውቅም አሁንም በድጋሚ ሰዎች ይህንን መጽሃፍ እንዲያውቁ ለማድረግ ይህንን ቃለምልልስ በማድረግህ ኣመሰግናለሁ። ወደፊት ከ ተጨማሪ ኣንባቢያን ኣስተያየት እጠብቃለሁ።

በውጭ ሀገር ለሚወለዱና ለሚያድጉ ልጆች የወላጆቻቸውን ቋንቋንና ባህልን የማወቃቸውን ጥቅም እንዴት ታዪዋለሽ?

ቋንቋ ባሕልን ታሪክን የሕዝቦችን መንፈሳዊነትንና ባሕርይን ለማሳወቅ የሚጠቅም መሣሪያ ነው። በተጨማሪም በያንዳንዱ ሰው ላይ የግል ማንነት ላይ ተፅ ዕኖ ፈጣሪም ነው። በውጭ የሚኖሩ ልጆች በወላጆቻቸው አፍ መፍቻ ቋንቋ መናገር መቻል ወላጆቻቸውን በደንብ ለመረዳት ከመቻላቸውም በላይ ቀደምት ማንነታቸውንም ለመረዳት ያስችላቸዋል ብዬ አስባለሁ። በጥቅሉ ቋንቋን መማር ልጆች  የአዕምሮ ብስለት እና የፈጠራ አቅም እንዲኖራቸው ያግዛል።


ልጆቻቸውን አማርኛ፣ ትግርኛ፣ ወይንም ግዕዝ ለማስተማር ለሚፈልጉ ወላጆች የምይትሰጪው ምክር ምንድነው?
የፊደል ገበታን መሸምደድ ለሁሉም ልጆች የሚሆን አይደለም ስለዚህ ልጆች እየተዝናኑ እና በፍላጎት የሚማሩበትን መንገድ መፈለግ የተሻለ ነው።

ለምሳሌ በፊደሉ ጨዋታ መፍጠር፣ ዕደ ጥበብ ወይንም ቅርፃ ቅርፅ ማዘጋጀት፣ ፊደላቱን በሰውነት ክፍላቸው እንዲሰሩት ማድረግ፣ ወዘተ ወይንም በአንድ ጊዜ ሁለት ነገሮችን ላይ ብቻ ማተኮር። ወይንም የጋራ ባሕሪያት ያላቸውን ፊደሎች አንድ ላይ በማድረግ ማቀናጀትና ምን እንደሚለያቸው እንዲገነዘቡ ማድረግ ። ለምሳሌ በ፣ ቨ፣ ሰ፣ ሸ ወይንም የ፣ ደ፣ ጀ፣ ጸ፣ ወዘተ. በአንድ ጊዜ አንድ ወይንም ሁለት ነገሮች ላይ ብቻ ማተኮር, በ, ሰ, ሸ, ቨ or የ, ደ, ጀ etc.  በሚወዱት ነገር ላይ ማንበብና መፃፍን ማበረታታትም በጣም ጠቃሚነት አለው። በመጨረሻ ልለው የምፈልገው የቆየ የፊደል መማሪያ ዜማ ሀ ሁ ሂ ሃ ሄ ህ ሆ  አቡጊዳ ሄውዞ መረሳት የለበትም

ዳንስ አቀናባሪ እና ተወዛዋዥ እንደሆንሽ እናውቃለን ኢትዮጵያ ባሕል ኑቬ ኤክፖዜ የዳንስ ቡድን እንዳስተዋወቅሽም ምስክር ነን፣ ይህ መጽሐፍ የዛ ጥረትሽ ቀጣይ ክፍል ነው?

በማኅበረሰባችን ውስጥ ብዙዎች በዳንስ ፣ በዳንስ አስተማሪነት፣ እና በዳንስ አቀናባሪነት ያውቁኛል። ኣሁን የሁለት ነገሮችን ሁ ሉለማወቅ የሚፈልጉ ፈጣን ልጆች እናት እንደመሆኔ መጠን አሁን ከባለቤቴ ጋር በ ተረተር ፕሮዳክሽን Two Ways To Heaven የሚል ፊልም ሠርተናል (በዩቱብ ይገኛል) )  http://TwoWaysToHeaven.TereTereT.com)በተጨማሪም ለብዙ ከያኒያን፣ ለበዓላት ዝግጅቶች እና ለኮሙኒቲ ቢዝነሶች ድረገፅ እየሰራሁ ነው

 የሕይወትን  ጥልቀት በተለያዩ መንገዶች መመርመር እወዳለሁ እያንዳንዱ ጥረት ደግሞ ካለፈ ግዜ ከዛሬ እና በአካባቢዬ ካሉ ጋር ግንኙነት ለመፍጠር እድል ሰጥቶኛል።

ይህ መጽሐፍ፣ “Ethiopic Alphabets : ፊደላት” ከልጆቼጋ የበለጠ ቁርኝት እንድፈጥር መንገድ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ለሌሎች ቤተሰቦችም በዚ መልኩ እንደሚረዳ ዕምነቴ ነው።

ኣመሰግናለሁ

እኔም ኣመሰግናለሁ

Ethiopic Alphabet – ፊደላት መጽሃፍን ለማግኘት ኣማዞን ላይ መግዛት ይችላ ሉ

Yohannes Ayalew

Related Posts

Leave a Reply

Read also x