Window of Forgiveness New Book By Emebet Mengiste የይቅርታ መስኮት አዲስ መፅሀፍ በደራሲ እመቤት መንግስቴ

ኑሮዋ በአሜሪካ ነው ። በአጣዳፊው የሰሜን አሜሪካ ህይወት ውስጥ ሆና ስድስተኛ መፅሀፏን አጠናቃለች ደራሲ እመቤት መንግስቴን “የይቅርታ መስኮት” ስለተሰኘው ስለ አዲሱ መፅሀፏ ቃለምልልስ አድርገንላታል::

ኢትዮፊደል: ሰላም! እመቤት በቅድሚያ እንኳን ደስ ያለሽ። ስለ አዲሱ​  መፅሀፍሽ ቃለምልልስ ስለተባበርሽን በ ኢትዬፊደል ሚዲያ ቤተሰቦች ስም እናመሰግናለን።   

‘Windows of Forgiveness’ ወይም በአማርኛው ‘የይቅር ባይነት መስኮቶች’ ስለተሰኘው አዲሱ መጽሀፍሽ አጠር ያለ ማብራሪያ ልትሰጪን ትችያልሽ? ከዚሁ ጋር ተያይዞ ይህን መጽሀፍ ለመጻፍ ያነሳሳሽ ነገር ምን እንደነበር እና የመጽሃፉን ይዘት ስለ ፍቅር እና ይቅር ባይነት ለማድረግ መነሻ ስለሆነሽ ነጥብ ላይ አተኩረሽ ብታብራሪልን። 

ደራሲ እመቤት : በቅድሚያ ስለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ። እንደምታውቁት የይቅርታ መስኮት 6ኛ መጽሐፌ ነው። ከዚህ ቀደም ለአንባቢ ባቀረብኳቸው ስራዎቼ ውስጥ ሁሉ ለማህበረሰባችን መነጋገሪያ በር ይከፍታሉ ብዬ ያሰብኳቸውም፤ ከዚያ ሲያልፍ ደግሞ በወቅቱ አስፈላጊ ግን ደፍረን የማንወያይባቸውን ሐሳቦች ይዤ ቀርቤ ነበር። የይቅርታ መስኮትም በይዘቱ ከዛ ብዙ አይለይም። ስለ ፍቅር እና ፍቅር ውስጥ ስላለው ይቅርባይነት የሚተርክ ስራ ነው።  

ይሄን መጽሐፍ እንድጀምር ያረጉኝ ሁለት አጋጣሚዎች አንድ ላይ ተከስተው ነው። በምኖርበት አሜሪካ ብዙ ግዜ አብረው የኖሩ አብረው ያደጉ፣ የተጋቡ፣ የወለዱ አለበለዚያም ከአንድ እናትና አባት ተወልደው እህትማማች፣ ወንድማማች የሆኑ ሰዎች፤ አብረው በፍቅር የኖሩበትን ዘመን እየረሱ፤ አይኑን እንዳላይ አይኗን እንዳላይ ሲባባሉ በተደጋጋሚ ስላየሁና፤ ከቀን ወደ ቀን ቁጥሩና ጉዳቱ እየጨመረ መምጣቱን በመረዳቴ ስለ ይቅርታ ለመጻፍ ወሰንኩ።  

ከየት እንደምጀምረው ሳሰላስል ደግሞ አንድ የሚገርም ጥቅስ አገኘሁ። “እውነተኛ ይቅርታ ስለነበረን መልካም ግዜ ከልብ አመሰግናለሁ ማለት ስንችል ነው” የሚል -ኦፕራ ዊንፍሪ

የይቅርታ መስኮት የተወለደው ከነዚህ ነገሮች ነው። አብረን መጓዝ ባንችል እንኳን፤ አብረን የነበረንን ግዜ ደምስሰንና እረግጠን ለጥላቻ በር ከፍተን አንዳችን ሌላውን እያደማን በዚያ ከምንደሰት በይቅርታና በፍቅር እንታከም የሚል ጽንሰ ሐሳብ ይዟል።  

ኢትዮፊደል: አሜሪካ እንደሚኖር አንድ ደራሲ፣ ስለ ፍቅር እና ይቅር ባይነት ይዘት ያለው መጽሀፍ ለመጻፍ የገፋፋሽ ነገር ምን ነበር? ይህ መጽሀፍ ወደ ዲያስፖራው ማህበረሰብ ሰርጾ ይገባል(resonate) ያደርጋል ብለሽ ያሰብሽበትን ምክንያት ብታስረጂን።

ደራሲ እመቤት: ፍቅር ለሁሉም ሰው የተሰጠ ታላቅ ስጦታ ነው። እንደ ውብ አበባ ፈካ ብሎ ልባችንን እንዲያስደስት፤ መኮትኮት ውሀ ማጠጣት፣ መመገብ የሁላችንም ተራ ነው። ያንን ካላደረግን ደግሞ እንደ ጥላቻ እሾሁ በዝቶ እንዲወጋን እናረገዋለን። ምርጫው የኛ ሆኖ ሳለ አመራረጡን ግን ብንነጋገርበት አይከፉም የሚል ትልቅ ሐሳብ አለኝ።  

ማንም ሰው ያለ ፍቅር መኖር አይመርጥም። ግን አካባቢያችን ያንን ካላሳየን ወይም የመጣንበት መንገድ ከፍቅር የራቀ ከሆነ እኛም ወደዛ ማምራታችን አይቀርም።  

መጽሐፉ ለደያስፖራው ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጆች ሁሉ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም ይቅርታ በአፍ ብቻ የሚነገር ቃላት ብቻ ሳይሆን ከልብ የሚመነጭ እና የተጎዳውንም የጎዳውንም ከእስራታቸው መፍታት የሚችል ትልቅ ሐይል ስለሆነ የሰው ልጅ በሙሉ ሊጠቀምበት እና እራሱን ነጻ ሊያወጣበት ይገባል ብዬ አምናለሁ። 

ኢትዮፊደል: የሙሉ ሰአት ስራ እየሰሩ ጎን ለጎን 6 መጸሀፍ መጻፍ ማለት ምንያህል ሊከብድ እንደሚችል ይታወቃል። ስለዚህ የተሳካ የጊዜ አጠቃቀም ኖሮሽ እንዴት የመጻፍ ጥረትሽን እንደገፋሽበት ብታጋሪን።

ደራሲ እመቤት: ከምንም ነገር በላይ የሰው ልጅ ለሚፈልገው ነገር ግዜ አያጣም። የሚጠጣው የመጠጫ ግዜ፣ ስፖርተኛው ለስፖርቱ፣ የፌስቡክ እና ቲክታክ አፍቃሪው፤ ፖለቲከኛውም እንደዛው። የኔ ምርጫ ማንበብ እና መጻፍ ነው ስለዚህ ግዜዬን በርከት አርጌ ለዛ እሰጣለሁ።

ሁለተኛ ደግሞ ከሰኞ እስከ አርብ በቀን ውስጥ 30 ደቂቃዎችን ያለ ምንም ማወላወል ለጽህፈት ብቻ ወስኜ አስቀምጫለሁ። የምጽፈው ነገር ባይኖረኝ እንኳን ያችን ሰላሳ ደቂቃ ወይ የቆየ ስራየን ሳርም ወይ ስሞነጫጭር አሳልፉለሁ። ለዚህ ይመስለኛል እዚህ የደረስኩት። 

ኢትዮፊደል: 6ተኛውና የቅርብ ጊዚው መጸሃፍሽ፣ ከቀደሙት መጸሀፎች የተለየ ሃሳብ እና አቀራረብ ይዞ መቷል? መጸሃፉን በመጻፍ ሂደትስ እግረመንገድሽን ምን አይነት ትምህርቶች ልትወስጂ ቻልሽ?

ደራሲ እመቤት: በርግጥ የኔ በርካታዎቹ ስራዎቼ አጫጭር ታሪኮችና መጣጥፎች ላይ ነው። በዛ መልኩ ካየነው ይሄ የመጀመሪያዬ ባይሆንም ሙሉ ልብ ወለድ ነው። ከሌሎቹ ስራዎቼ የሚለይበትም የሚመሳሰልበትም ብዙ ነገር አለው።  

“እውነተኛ መምህር ሁሌም ተማሪ ነው” ይባላልና፣ እኔ ዘላለም ተማሪ ነኝ ብዬ አምናለሁ። በማንበብ ከተማርኩት እኩል ከመኖርም ተምሬአለሁ። ከምጽፉቸው ነገሮች የመጀመሪያዋ ተጠቃሚ እኔ ነኝ። ይሄንን መጽሐፍ ስጽፍ በጣም ብዙ ነገሮች ተምሬአለሁ። ከሁሉም በላቀ የፍቅርን ሃያልነት፣ የይቅርታን ጉልበት፣ እንዲሁም ሁለቱም ለሁላችንም የተሰጡን ታላቅ ስጦታወች መሆናቸውንና፤ በሆነ ባልሆነ ምክንያት ከኛ የራቁ ቢመስለን እንኳን እራሳችንን በርብረን ልናገኛቸውና ልናሳድጋቸው እንደሚገባ ተምሬበታለሁ። 

ኢትዮፊደል: እስካሁን የመጣሽበትን መንገድ በማሰብ፣ የተለያዩ ሀላፊነቶች ላይ ለሚገኙ ጀማሪ ጸሀፊዎች በተለይም ለመጻፍ እና ማንበብ ጊዜ እና ተነሳሽነትን ስለ ማግኘት ምን ትመክሪያለሽ? 

ደራሲ እመቤት: የሰው ልጅ ዋና ሀብቱ ጊዜ ነው። ጊዜአችንን ለምን እንደምንሰጥ ማወቅ ግድ ይላል። በቀን አንድ ገጽ ማንበብ ወይ ደግሞ በቀን አስርና አስራ አምስት ደቂቃ ለጽሕፈት መስጠት ብንጀምር እራሳችንን ቀስ በቀስ ወዳሰብነው እንድንደርስ ማረግ እንችላለን።  የኔ ምክር ሁልግዜም አንድ መስመርም ብትሆን ጻፉ። እራሳችሁን የማንበብና እና የመጻፍን ነጻነትን አትንፈጉ ነው። 

ኢትዮፊደል: ተጨማሪ መጸሀፎች ለመጻፍ ታስቢያለሽ ?

ደራሲ እመቤት: አዎ በሚገባ! መታተም የሚለውን የአምላክ ፈቃድ ይጨመርበትና። እኔ ግን የሆነ ነገር ካልጻፍኩ ቀኑ ይከብደኛል። መጻፍ የማቆም ፍላጎት የለኝም።

ኢትዮፊደል: አንባቢያን ይህን መጽሀፍ የት ማግኘት ይችላሉ?

ደራሲ እመቤት: መጽሐፎቼ አማዞን ላይ ይገኛሉ። ከዛ በተጨማሪ ደግሞ አፍሮሪድ አፕልኬሽን ላይ ኢቡክ እና ትረካዎች ይገኛሉ።  

የይቅርታ መስኮት አማዞን ላይ ማርች 15 ይገኛል። 

እኔን ደግሞ emebet1974@gmail.com emebetbooks.com ላይ ታገኙኛላችሁ። 

Photos by Emebet Mengiste

ትየባ በ ማህሌት ፈቃዱ

for more stories check our YouTube channel here https://youtube.com/@ethiofidel?si=-buab0_9wIbdU5N-

Yohannes Ayalew

Related Posts

Leave a Reply

Read also x