ትውልደ ኢትዮጵያዊው ካናዳዊ  ዶ/ር ኃይሌ ፈንታ ለቶሮንቶ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ የአእምሮ ጤና ላበረከቱት አስተዋጽኦ የ እውቅና ሽልማት ተበረከተላቸው

ትውልደ ኢትዮጵያዊው ካናዳዊ ተመራማሪ ዶ/ር ኃይሌ ፈንታ በቶሮንቶ የሚገኙ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላትን የ የአእምሮ ጤና  ለማሻሻል ላበረከቱት አስተዋጻኦ የእውቅና ሽልማት ተበረከተላቸው፡፡

 በቶሮንቶ የአእምሮ ጤና ላይ አተኩሮ የሚሰራው ኢትዮ ካን ብሪጅ ዘ ጋፕ ባዘጋጀው የአእምሮ ጤና ዝግጅት ላይ ነው ዶ/ር ሓይሌ ፈንታ ሽልማት የተሰጣቸው፡፡

ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በአእምሮ ደህነነት እና ሌሎች የጤና ጉዳዮች ዙሪያ በርካታ ጥናትና ምርምሮችን አካሂደዋል፡፡

ወደ ካናዳ ከመምጣታቸው በፊት በኢትዮጵያ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ዋና የጤና መኮንን በመሆን  የሰሩት ዶ/ር ሓይሌ በ ካናዳ ማጊል ዩኒቨርሲቲ በኢፒዲሞሎጂ የፒኤችዲ ዲግሪያቸውን  ከዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ በ ፓብሊክ ሄልዝ ማስተርስ ዲግሪያቸውን ሰርተዋል ፡፡ 

ዶ/ር ኃይሌ በቶሮንቶ የሱስ እና የአእምሮ ጤና አገልግሎቶች ማእከል (CAMH) ውስጥም ለ አመታት ሰርተዋል። በቶሮንቶ የኢትዮጵያ ማህበር ፕሬዝዳንት በመሆንም ማህበረሰባቸውን በ በጎ ፍቃደኝነት አገልግለዋል።

  የ ኦንታሪዮ አእምሮ ጤና ምክትል ሚኒስትር እና የፓርላማ አባል ማይክል ቲቦሎ እንደዚህ ያሉ የአንጋፋ ተመራማሪዎች አስተዋፅዖ  ለ የባህሉ ተስማሚ አገልግሎቶች ለመስጠት ትልቅ መሠረት ይጥላል ብለዋል፡፡ እውቀትን ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡  “ከልጆቻችን ጋር እውቀትን ለመካፈል የምናጠፋው ጊዜ የልጆችንአቅምን የሚያጠናክር ነው። አሉታዊ ነገር ሲገጥማቸው ወደ ኋላ የሚመለሱበት 

ነገር ይኖራቸዋል” ብለዋል ሚኒስትር ቲቦሎ።

ዶ/ር ቃል በላይ፣ ዶ/ር አልፋ አበበ እና ዶ/ር ዮሓንስ ታደሰ ጨምሮ ሌሎች ተናጋሪዎች ዶ/ር ኃይሌ በ ማህበረሰቡ ውስጥ ያደረጉትን አስተዋጽኦ አድንቀው ይህንን የሳቸውን ተግባር የአሁኑ እና መጭው ትውልድ ሊቀጥልበት ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የመሠረተ ልማት ሚኒስትሩ የፓርላማ ረዳት ቪጃይ ታኒጋሳላም እንደዚህ ያሉ ዝግጅቶች የአእምሮ ጤና ጉዳዮችን እንደየባህሉ ለመፍታት የህብረተሰቡን አቅም ያጠናክራሉ ብለዋል ።  መንግስት በ ስካርቦሮ የህክምና ትምህርት ቤት እየገነባ መሆኑን ይህ ትምህርት ቤትም ከ1841 ጀምሮ በቶሮንቶ የመጀመሪያው የህክምና ትምህርት ቤት እንደሆነ ጠቅሰዋል

በ ካናዳ የሚኖሩ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ማህበረሰቦችን ጨምሮ የአፍሪካ ካሪቢያን እና ጥቁር (ኤሲቢ) ማህበረሰቦች በአእምሮ ህመም በ ከፍተኛ ደረጃ  ተጎጂ ናቸው 60% ያህሉ የጥቁር ማህበረሰብ አባላት ለአእምሮ ህመም የተጋለጡ ሲሆኑ 23% የሚሆኑ የአፍሪካ እና ካሪቢያን ተወላጅ ወጣቶች ወደ አእምሮ ህክምና አገልግሎት የሚመጡት በፖሊስ ነው።

በዝግጅቱ ላይ ኢትዮጵያዊው ካናዳዊ የስነ አእምሮ ሃኪም ዶ/ር ሰሚር ቡሌ ባቀረቡት ገለጻ ፀረጥቁር ዘረኝነት፣ መገለል እና የህክምና አቅርቦት ውሱንነትን ለዚህ እንደ ዋና ምክንያቶች ጠቁመዋል።

ዶር ቡሌ ህብረተሰቡ የአዕምሮ ጤና አገልግሎትን ለማግኘት ፍቃደኛ እንዲሆን የህብረተሰቡን ድጋፍ እንዲጠቀም እራሱን እንዲከባከብ አሳስበዋል “እባካችሁ እርዳታ ለመጠየቅ በጭራሽ አትሸማቀቁ” ሲል ተናግሯል።

የታይቡ የማህበረሰብ ጤና ማእከልዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሊበን ገብረሚካኤል በመዝጊያ ንግግራቸው በህብረተሰባችን ውስጥ በአእምሮ ጤና ዙሪያ 

የሚደረገው  ውይይት መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

  ታይቡ ማህበረሰብ ጤና ማእከል ከኢትዮፊደል ፕሮዳክሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የአእምሮ ጤና ላይ ያተኮረ ዶክመንተሪ ፊልም በዝግጅቱ ላይ    ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

 የዝግጅቱ አስተባባሪ ፀደይ ለገሰ በተለይ ከ ኢትዮፊደል ጋር  ባደረገችውቃለምልልስ ዝግጅቱ ህብረተሰቡን በማሰባሰብ በአዕምሮ ጤና ጉዳዮች     ላይ ለመወያየት ጥሩ መድረክ ነው ብላለች።

በቶሮንቶ በተካሄደው የጥቁር አእምሮ ጤና ሳምንት አካል በሆነው በዚህ ዝግጅት ላይ በፎቶ ጋዜጠኛ ዳዊት ጥበቡ የተዘጋጀ የፎቶ ትርኢት ቀርቧል።

ፎቶዎች በዮሐንስ አያሌው ኢትዮፊደል

Yohannes Ayalew

Related Posts

Leave a Reply

Read also x